www.andnet.de

  • Increase font size
  • Default font size
  • Decrease font size
Home

ከተማን በደም ለሚሰራ ወዮለት! - ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail Print PDF

ለኢትዮጵያ ምድር ሰላምና ለሕዝቦችዋ ነጻነት የትጥቅ ትግል በምንም ዓይነት መልኩ አማራጭ መንገድ ሊሆን እንደማይችል ቀደም ስል ባበረከትኳቸው በርከት ያሉ ጽሑፎችና እንዲሁም ብዙሐኑ ሀገር ወዳድ በውስጥም በውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያውን በብዕራቸው አማካኝነት በአፅንዖት ገልጸዋል እነሆም በተጠናከረ መልኩ ለኢትዮጵያ ምድር ብቸኛ መፍትሔው ሰላማዊ ትግል መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።

ወደ ዝርዝር ሐተታዬ ከመዝለቄ በፊት በማስቀደም ሁሉም እንደ ደመና ሲበተኑ እንደ ጥላ ሲያልፉና እንደ መጎናጸፍያ ሲያረጁ ዘመናትን እያሳለፈ ዘመንን ተሻግሮ የሚሻገር መጻህፍትን ተንተርሼ ወቅቱን እና ሰዓቱን አስመልክቼ ግላዊ አመለካከቴን የማንጸባርቅበት ትልቅ ዕድል በማግኘቴ የሰዎች ነጻ ሃሳብ ለማንሸራሸር ስለ ተደራጁ የአማርኛ-እንግሊዝኛ ድህረ ገጾችን ከልብ ለማመስገን እወዳለሁ። በመቀጠል ታላቁ የዓለማችን ፀሐፌ ተውኔት ዊልያም ሼክስፔር “የእውነት መጨረሻ ቁጣ ነው” እንዳለው ምንም በጥቂቶች ዘንድ የማይፈለግ ፀጉር የሚያስነጭ መራር መልዕክት ቢሆንም በዛሬው ዕለት ሁላችንን ሀገር ወዳዶች ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ያደርገናል፤ ሀገራችንም በገዛ እጃችን ከማውደምና ከማፍረስም ይተርፋ በማለት “ከተማን በደም ለሚመሰርት ወዮለት!” በሚል ርዕስ ተመልሼ መጥቻለሁ።

አንባቢ ሆይ! ልንሰማው የሚገባን እውነት ሆኖ ሳለ መስማት ስለማንፈልገው ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮች እያነሳሁ ማተቴ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል በመዘንጋት አይደለም። ስላለኝ የተገለጠ ክርስቲያናዊና ፖለቲካዊ አቋም ግልጽ ባለመልኩ ሳስቀምጥና ስገልጽም ይህን ተከትሎ ሊመጣብኝ ስለሚችለው አለመግባባትን የሚፈጥራቸው ሁሉ ግምት ውስጥ በማስገባትና ኃላፊነት በመውሰድም ጭምር ነው። በመሰረቱ በምንም ዓይነት ሞቲቭ ይነገር ከማንምም አፍና ብዕር ይውጣ ይፃፍ የሚረባና የሚጠቅም ገንቢ ሂስ እስከሆነ ድረስ ነቀፋና ወቀሳ የምጠላ በረባም ባልረባም የተወለድኩባት ቀን የምራገም ዓይነት ሰውም አይደለሁም።
የሚረባኝኝ ስቋጥር አላስፈላጊ ሆኖ ያገኘሁት ደግሞ በፈገግታ አልፈዋለሁ ለምን? የመጻፍ መብቴን ተጠቅሜ የማምንበትን በነጻነት መልዕክቴን እንዳስተላለፍኩ ሁሉ ማንም ጽሑፌን ያነበበ አካል ደግሞ ያመነበትን የማለትና ምላሽ የመስጠት ባለ ሙሉ መብት ነው ብዬ ስለማምን ነው። ይህ በእንዲህ ሆኖ ሳለ ግላዊ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ አመለካከቴን ተከትሎ ባልተገራ ብዕር ስለሚጻፉ ጥበብን እና ማስተዋልን እጅግ ስለተለዩባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው በኢ-ሜይል አድራሻዬ ስለ ሚላኩ ዛቻዎች ማስፈራሪያዎችና ልክ የሌላቸው ልቅ ስድቦች ሁኜ እስካልተገኘሁ ድረስ ሽንጤን ገትሬ ንጽህናዬን ለማረጋገጥ የምሞግትበት አንዳች ምክንያት እንደ ሌለኝ ስገልጽ በታልቅ ትህትናና አክብሮት ነው።

ወደ ተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስመለስ ሰው ወዶ የሰው ደም ደም አይሸተውም! እላለሁ “እኔ ካልገዛሁ” “እኔ ካልነገስኩ “እኔ ካልመራሁ” “እኔ ካልታየሁ” ብቻ “እኔ እኔ…” ማለት በሰው ልብ ሲነግስ ከተማን በደም ለመመስረት ስለሚነሳሳ እንጂ። ቢሆንም ጥያቄው በነፃነት ሽፋን የትጥቅ ትግል እየተባለ ለምን በንጽሐን እና ድሀ አደግ ዜጋ ደም ቁማር መጫወት አይቆምም ነው። የግለሰቦች ጥማት ምኞትና ድካም የመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥማትና ፍላጎት ተደርጎ የሚቀርብበት ምክንያቱ ምንድ ነው? ስህተት ወይስ ድፍረትና ንቀት? የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህረ ምርጫ 1997 ዓ/ም ጀምሮ የሚረባውንና የማይረባውን ለመለየት በማይቸገርበት ሁኔታ ጥሩ ትምህርት የቀሰመ ዜጋ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ከቆረጡ ጥቂት ግለ ሰቦች ጋር አብሮ ተስፋ የመቁረጥ ግዴታም የለበትም። ደግሞስ ካለፈው የውስጥም የውጭም እውነታዎች (ታሪኮች) ላለመማር ለምን ራሳችንን ንፍጎች አናደርጋለን። የትኛውና በየትኛው የዓለማችን ክፍል የሚገኝ መንግሥት ነው በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ ወጥቶ ለሕዝቡ ሰላምንና ዕረፍትን የሰጠ? ከቀድሞ የባሰ እንደሆነ እንጂ።

ሰላማዊ በሆነ መንገድ በጽናት ታግለን ግላዊና ሀገራዊ ነጻነታችንን ማወጅ እደሚቻል በዙሪያችን እንደ ደመና የከበቡን ብዙ ምክንያቶች አሉን። ወገኖቼ ሰላማዊ ትግል ምን ማለት እንደ ሆነ ይገባን ዘንድ ይህን ማወቅ ይጠበቅብናል ሰው የሰው ጠላት እንደሌላው የሃሳብ ጠላት እንጂ። ሃሳብን ደግሞ በሃሳብ ለማሸነፍ ብቁ ሆነህ መገኘት እንጂ የሰውን ደም ለማፍሰስ ታንክና መትረየስ ማሰለፍ ተገቢ ነው ቢዬ አላምንም። የወያኔ መንግሥት የኃይል አገዛዝ የሀያልነት መገለጫ ሳይሆን የሽንፈት ምልክት ነውና። ክፉ የራሱ ባልሆነ፣ ባልተሰጠው ነገር ድርቅ ማለትም የባህሪው ነው የክፍዎችን መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ለመግታት በመንገዳቸው ሳይሆን በማይፈልጉትና ባልተበቁት መንገድ ድርቅ ብለን በመገኘት ነው የያዘውን ማስጣል የምንችለው።

የትጥቅ ትግል አራማጅ ወገኖች ሆይ! አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሰላማዊ ትግል ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ከባርነት እና ከአንባገነናዊ የወያኔ አገዛዝ ነጻ ማውጣት የማይቻል መስሎ ቢታያችሁም እንኳ ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት ጥለን ማለፍ ይገባናል በማለት በመልካም አርአያነታችሁ ምሳሌ መሆን ሲገባሁ በነጻነት አውጪዎችና በሀገር ወዳዶች ሥም አገር በቀል አጥፍቶ ጠፊዎች መሆን እጅግ አሳዛኝ ገጽታችሁ ሆኖ ሳለ አስከፊ የምድራችን ታሪክ በተወሳ ቁጥር ትውልድ እየረገማችሁ እንደሚኖርም ማወቅ ይገባቹኃል። ይህም ብቻ አይደለም ዜጎችን ጥይት አስታጥቀህ ወደ (እሳት) ወደ ጦር ግንባር መሸኘትም ከራስና ከልጅ እንደሚጀምርም በዚህ አጋጣሚ በአንክሮት ለመግለጽ እወዳለሁ።

ድህነትን እና ሥራ አጥነትን ያደከውም ህይወት ሸክም የሆነችበትን ሀገር ተረካቢው ወጣት ትውልድ በመጠቀም ወጣቱ ትውልድ የእሳት ራት ሲሆን ጊዜና ዕድል የሰጠው ደግሞ ከተደበቀበት ኩሽና ቤት እየተፈለፈለ በሚስኪኖች ደምና አጥንት ተረማምዶበዙፋን ላይ ይቀመጥ ማለትም ሚዛናዊነት የጎድለው አስተሳሰብ ከመሆኑ በላይ ፍጹም አረመኔነት የተሞላው ርካሽ አመለካከት ነው። ለነገሩማ የተዘራ ሁሉ እንደማይበቅል “የተማረና” ሥም ያለውም ሁሉ ማስተዋልና ጥበብ አለው ወይም ይኖሯል ማለት እንዳልሆነ ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 6 ላይ በሚገባ አስተምረዋል።

አንድ ሌላ ልብ ሊባል የሚገባውን ነጥብ ላክልና ለዛሬ ያዘጋጀኋትን አጭርና ግልጽ መልዕክቴን ላገባድድ። ይኸውም የሀገሬ ሰው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አለች አህያ በማለት እንደ ሚተርተው አሥር ጊዜ የትጥቅ ትግል የትጥቅ ትግል ሲባል ልብ ማለትና ማስተዋል የሚገባን ነገር ቢኖር የትግሉ አራማጅ ኃይሎች ነገር ዓለማቸው ሁሉ በኃይል እና በጉልበት ለማቅናት ደፋ ቀና ሲሉ ከሥር ደግሞ በሰለጠነው ዘመን በጠረጴዛ ዙሪያ የማያምን፣ ሁሉን ነገር በጉልበት ለማከናወን የሚገሰግስ፣ ጠበንጃን እንደ ስክርፒቶ የማይታጣበትና የማይለየው አዲስ ትውልድ እያፈሩ እንደሆነም መዘንጋት የለብንም

ዓመት ሁለት ዓመት የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ዞር ዞር ብለን የልባችን ስላልተሳከልን ብቻ ለግል ለስኬታችን የምንቀይሰው አጥፊ መንገድ ትክክል አይደለም። በኩርፍያ የምንለውጠው ታሪክ የለም! ዓመታትም ቢፈጅ በነገር ሁሉ ጽናትን ያስፈልጋል። ይቅር በሰፊው ሕዝብ ጉዳይ ላይ በግል ህይወታችን ለምናመጣው ሥር ነቀል ለውጥ (ስኬት) እንኳን ሳይቀር ጽናት ምን ያህል ቁልፍና አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ኮንፒተርን ከፍቶ ይህን ማንበብ ለቻለ ግለሰብ ሰፊ ማብራርያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። የማይቻለውን ይቻላል በማለት ብዕሬን አላነሳም አላፈጥጥም። ለቀናትና ለወራት ብቻ ሳይሆን ለዓመታት ለሰው አእምሮ በማይመች ከባድ ሁኔታዎችን አልፌ ዛሬን ማየት መቻሌን ሳስበው ይህን ለምጻፍ ድፍረቱን ሰጠኝ። ከብት ነው በባህሪና በተፈጥሮ የሚመስሉትን ከብቶች ለመቀላቀል ሰላምታ መስጠት የማይጠበቅበት እንጂ ለግል ነጻነታችንም ሆነ ስለ ሰፊው ሕዝብ አስመልክተን ለምንከፍተው አጀንዳ መንገዱ ሊያስከፍለን የሚችለውን ዋጋ ተምነን ጸንተን መታገልን እንደሚገባን አሜን ብለን አምነን መቀበል በውዴታ የምንቀበለው ነገር ብቻም ሳይሆን ግዴታችን መሆኑን ጭምር አምነን እንድንገባበት ነው የሚጠበቅብን። በከፈልነውና ገና በትግሉ መስመር እስካለን ድረስ በምንከፍለው ዋጋ ማንንም ተጠያቂ አናድርግ።

ክቡር ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ! ወደድንም ጠላንም ዛሬ በዚሮ ተባዝተን ይቅር በስደት ምድር በገዛ ምድራችን እንደ ባሮች ሆነን ኑሮአችን እየገፋን የምንገኘው የዚህ የተሳሳተ “የትግል” መስመር ቀጥተኛ ተፅዕኖና ውጤት ነው። የሁላችን ጥያቄ ሆኖ መነሳት የሚገባው አስፈላጊ ነጥብ ቢኖር የምድሪትዋ ዘር የመጣውን ሁሉ ለፖለቲካው ፍጆታውና ለግል መሻቱ መጠቀምያ የሚያውለው እስከ መቼ ነው? ማለት ይኖርብናል። በአንድም በሌላም አንበጣ ደጎብያና ኩብኩባስ በሉን መድኃኒት ባልጠፋበት በሰለጠነው ዘመን ተምችም አይቅርብን ከሆነ ቋንቋ ግልጽ እናድርገው።

ትናትን አበላሽተው አፈራርሰውና አተረማምሰው ወደ ሥልጣን የወጡ የትናንት ኃያላን ዛሬ ደግሞ በተራቸው ተበላሽተው ፈራርሰውና ተተረማምሰው በታላቅ ጭብጨባ ወደ ሥልጣን እንዳልወጡ አንገታቸውን ደፍተው በታላቅ ህፍረትና ውርደት እንደ ተሸኙ ሁሉ የወያኔ መንግሥት ከሥልጣኑ ማስወገድ ብቸኛ አማራጭ መንገድ የትጥቅ ትግል ነው የምትሉ ወገኖችም እንደሆነ ከአማራጭ መንገዳችሁ በተጓዳኝ ይህን ከላይ የተመለከትነውን እውነታ ደግሞ አምናችሁ መቀበል ይጠበቅባችኋል።
ያለፉትንም ሆኑ ያሉትን መንግሥታት ባጠፉት ጥፋት በሕግ ፊት ይቅረቡልን ስንል በነጋ በጠባ ቁጥር ሥራ ፈትተን ሥራ ሰርተው በተለወጡ የምዕራባውያን ጎዳናዎች ምላሳችን ከትናጋችን እስኪጣበቅ ድረስ ጭሆታችንን የምናቀልጠው አጥፊዎች ሥራቸውና ድርጊታቸው ሁሉ መነሻው ህዝብን እና ሀገርን እናቀናለን ከማለት የመነጨ እንጂ የኢትዮጵያ ምድር ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት አልነበረም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ከማን ምን መጠበቅ እንዳለብንና እንደሚገባን ለይተን እንወቅ! ነቢዩ ኤርምያስ በእስራኤል ህዝብና ምድር ስለሆነው ሁሉ ነገሮችን ከመሆናቸው በፊት እንደ እግዚአብሔር መልዕክተኛ አስቀድሞ የተቀበለውን መልዕክት ሳይቀንስም ሳይጨምርም መልዕክቱን ስለ ማስተላለፉንና ግዴታውን ስለመወጣቱ ሲናገር በእናንተ መካከል ለረጅም ዓመታት ተቀምጬ ስናገር አልሰማችሁኝም በማለት በምድሪትዋና በሕዝቡ ስለሆነው ስለ ደረሰው አሰቃቂና ዘግናኝ ውድመት ከልብ የተሰማውን ሐዘን ይገልፃል። ምንም ሁኔታዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየከፉና እየከረፉ ቢመጡም ስሜቶቻችንን ተከትለን እንደ አህያ ከሁለት ሜትር በላይ ማየት ተስኖን የምንወስዳቸው እርምጃዎች እና የምንፈጽማቸው ድርጊቶች ነገ መጠሪያ ሥማችንን ለመለወጥ እስክንገደድ ድረስ ውርደትና ኪሳራ ያሳጭዱናል።

እንክርዳድን ዘርተህ የስንዴ ምርጥ ዘርና ገብስ አይጠበቅም! ነውርም ነው። አንዳቸውም ከተማን በደም የመሰረቱ “ታጋዮች” መጨረሻቸው አላማረምና ከተማን በደም ለመመስረት ከመድከምም ሆነ ከተማን በደም ለመመስረት ከተነሱ ግለ-ሰቦች አብረን ከመሰለፍ፤ እኛ ለምድራችን ከምናስብላት በላይ የሰው አእምሮ ሊደርስበት ባልተቻለው ውብና ድንቅ ዲዛይን ምድሪትዋን ያበጀ ልዑል እግዚአብሔር ይጠብቀን።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Last Updated on Thursday, 24 June 2010 20:05  
<<  September 2010  >>
 Mo  Tu  We  Th  Fr  Sa  Su 
    1  2  3  4  5
  6  7  8  9101112
13141516171819
20212223242526
27282930   

Impressum


Free Ms. Midekssa

Fight for your Freedom



Get the Flash Player to see this player.

Free_Judge_Birtukan_Midekssa

Download
a Petition letter
>>HERE<<




Featured Videos

AllVideos Reloaded

Gavick Tab GK1

test


Newsflash

An Ethiopian Sentenced to Death Says He's Not Surprised by Sentence

Berhanu Nega, founder of the Ginbot 7 and former leader of the Coalition for Unity and Democracy, said he was not surprised by the death sentence. Read more...